Tidarfelagi.com

እንደምትወዳት ንገራት

ሕይወት የብድር በሬ፥ መቼ ሁሌ ይጠመዳል
ለጊዜው ብቻ የመጣ፥ ጊዜው ሲደርስ ይሄዳል
የተሰጠህ ጸጋ ሁሉ፥ ደሞ ካንተ ይወሰዳል።

ቀለበት፥ አምባር አይደሉም
እጅህ ላይ ሁልጊዜ የሉም
ቀናት ሳምንታት ወራት
ዛሬውኑ፥ አሁኑኑ፥ እንደምትወዳት ንገራት።
አበቦች ሁሉ ሳይረግፉ
ምኡዝ ሽታዎች ሳይጠፉ
ያጸድ በሮች ሳይቆለፉ
በንቦች ጎዳና ላይ፥ ተርቦች ሳይሰለፉ
በንፋስ ክንፍ ሳይመታ
ሕይወት የላምባ መብራት
አሁንኑ ዛሬውኑ፥ እንደምትወዳት ንገራት።

ርቃ ሳትገሰግስ
ገና ስንቋን ስትደግስ
እንዲሁ እንዳማረባት
ቀልብህ እንደቀረባት
መቃብር በመዳፉ
እንደጠጠር ሳይቀልባት
አፈሩን ሳትዛመድ
ወደማትቀባው አመድ
ወደማትስበው አየር
ሳትቀየር
አንትም አንደበት ሳለህ፥ እሷም ጆሮ ሳያጥራት
ዛሬውኑ! አሁኑኑ! እንደምትወዳት ንገራት።

2 Comments

  • Anonymous commented on March 26, 2022 Reply

    ድንቅ ግጥም ነው። አመሠግናለሁ በውቄ!

  • Sisay commented on March 26, 2022 Reply

    ድንቅ ግጥም ናት። አመሠግናለሁ በውቄ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *