Tidarfelagi.com

እያንዳንድህ ፥ እያንዳንድሽ!

ከናትሽ ሙዳይ ሰርቀሽ፥ ኮኮስ ቅባት የተቀባሽ
በጸደይ ወቅት ፥ የስሚዛ አበባ የጠባሽ
ድድሽን ባጋም እሾህ የተነቀስሽ
ጡትሽን ለማስተለቅ ፥አጎጠጎጤሽን በውሀ እናት ያስነከስሽ
ቤት ባፈራው ጌጥ ብቻ፥ በዛጎል በዶቃ ያማርሽ
በቃቃ ጨዋታ ወግ ፥ በሽቦ መኪና የተዳርሽ
ሲያደንቁሽ የተሽኮረመምሽ
ሲነኩሽ የተስለመለምሽ
ሲስሙሽ፥ አገር ለቀሽ ለመመነን ያለምሽ
በቸርቺል ጎዳና ላይ ፥ሰኞ ማክሰኞ የተጫወትሽ
የኔ ትውልድ አባል ነሽ
ብትኮሪ ምክንያት አለሽ።

እያንዳንድህ!
በጅምር አስፋልት ላይ ፥ ሽኩኔታ የነዳህ
ወይራ ከታጠነ ማድጋ ፥ በመርቲ ጣሳ የቀዳህ
በጥቂቱ የረካህ ፥ በመናኛው የተደነቅህ
ድንኳን ሰብረህ በቅልውጥ፥ የጎረቤት ሰርግ ያደመቅህ
ካባትህ ሽልንግ ሰርቀህ ፥ “ዲስኮ ዳንሰርን” ያየህ
ባስር ሳንቲም ፥ ትኩስ ሽልጦ የገበየህ
በየመስኩ፥ በየፈፋው ፥ፋንድያህን የነሰነስህ
በብሳና ቅጠል ፥ የጅራት ማብቀያህን ያበስህ
በችፍርግ ጥርስህን ያነጣህ
ከጆሮህ ውስጥ፥ ሰርጎ ገብ በረሮ ያወጣህ
በቃቃ ጨዋታ ላይ፥ የህልምህን ቆነጆ ያጨህ
ራስህን በቤሳ ምላጭ የተላጨህ
ፍቅረኞች ተቃቅፈው ሲሄዱ ፥ ስታይ እየተከተልህ ድንጋይ የወረወርህ
የሩፋኤል ቀን ታጥበህ፤ አመቱን ሙሉ ያደፍህ
በውሀ ቀጠነ የተገረፍህ
ከፖሊዮ በክትባት
ከብሄራዊ ውትድርና በብልሀት
የተረፈህ
ከገበሬ ማሳ ላይ ፥ በቆሎ እሸት የዘረፍህ
በዳጥና በሸርተቴ ፥ ቁምጣ ሱሪህን የጨረስህ
ስሚዛ ስር ተደብቀህ፥ የሲጃራ ቂጥ ያጨስህ
ጣትህን ለሙጀሌ የመገብህ
የኔ ትውልድ አባል ነህ
በትኮራ ምክንያት አለህ።
(ቆየት ካለ ስብስብ የተወሰደ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *