ምነው ፍጣሪዬ በህልም የመሰለኝን እራሱን ህልም አርገህልይ ያየሁት ነገር እውን በሆነልይ አልሁና ደግሜ ታስበው ግን ህልም ባይሆን ሻንቆ ሊጨርሰን እንደነበር ውል ትላለብይ እንኳንም ህልም ሆነ ፈጣሪዬ ይቅር በለይ ብዬ ተመልሼ ተጠቅልዬ ተኛሁ፣
ጥዋት ተንቅልፌ የነቃሁት ተረፈደ ነበር።ብድግ አልሁና ድምጥ ለመስማት ትሞክር ድምጥ የለም ለክፉም ለደጉም እክንዴ ላይ እጠመጠምኋት ፋሻ ላይ ሴንጢዋን ደበቅሁና ሽጉጡን ምቹ ሁኔታ መኖሩን ታረጋገጥሁ ቡሃላ መጥቼ ለመውሰድ ትላሰብኩ እዛው ሻንጣዬ ውስጥ ትቼው ወደ ሽንት ቤት ልገባ ተክፍሌ ትወጣ እሳሎኑ መሃል የተቀመጠውን ሰው በጨረፍታ ተማየቴ በወጉ መራመድ ተስኖይ እግሬ ተሳሰረብይ።ሻንቆ ሻንቆ ነው ! ሻንቆ ነው! እያልሁ ለራሴ ስሙን እየደጋገምሁ ወደ ሽንት ቤት ትገባ ተመታጠቢያ ቤት ድምጥ ትለተሰማኝ እትዬ እየታጠቡ እንደሆነ ገባይ።
ተሽንት ቤት ተወጣሁ ተዚህ ሰውዬ ጋር ፊት ለፊት መተያየቱ ትለማይቀርልይ ፍርሃት ፍርሃት ቲለኝ ቢሄድልይ ብዬ ታልወጣ ቆየሁ።እትዬ ተመታጠቢያ ቤት እንደወጡ ሰማሁና ግድ ቲሆንብኝ ወጣሁ።እትዬ እሳሎኑ መሀል ተገትረው ጠጉራቸእን ይነካካሉ ሻንቆን ፊት ለፊት ታየው ብርክ ያዘይ።ደሞ ምን አፍጦ ያየኛል ፈጣጣ።
ቁርስ ልስራ እትዬ? “ቁርሱን ተይውና ቡና አቀራርቢ በምሳ ሰአት ቁርስ ልስራ ትለኛለች እንዴ ቆርሶ ይጣልሽ!”ቲሉኝ ደሜ ፈላ በዛ ላይ ሻንቆ “ተያት እንጂ…ሃሃሃሃ” እያለ ቲያስካካ ይብሱን አንጨረጨረይ።
ቡናውን አቀራርቤ ተሁለቱ የሞት መንፈሶይ ፊት ለፊት ትቀመጥ ቀፈፈይ።
“እቺ በረሮ ልጅሽ ግን መቼ ነው እምትወፍረው ……ሃሃሃ ” አለ ሻንቆ ቁልቁል እየተመለከትይ።
የናቴ አምላክ አይንህን ያብረው እቴ ብርር ያርገው ደሞ በረሮ ይለኛል እንዴ ምን ይመስላል በሬ።
” ምን በረሮ ነች እቺ ተናዳፊ ጊንጥ መሆኗን ሰሞኑን ደረስኩበት እኮ ሻንቅዬ
በሷ ዙሪያ እማወራህ ይኖረኛል። አሉ እትዬ።
ገንጥሎ ይጣሎት እቴ የሚገነጥል ይገንጥሎት የሱ በረሮ ማለት ቲገርመኝ እኝህ ደሞ ጊንጥ ቲሉኝ ደሜ ተንተከተከይ። ሰውን ታይሞት በቁም የሚበሉ ምስጥ መሆኖትን ማን በነገሮ።ነገሩ ማን ደፍሮ ይነግሮታል ታንናገርም መኖር አልቻልንም።
“ተያት ባክሽ አሁን እቺ ምኗ ይናደፋል ፊታን አታይውም እንዴ ምንም አታውቅምኮ አዲስ አበባ ከመጣች አምስት አመት አልፏታል አደል? ግን ስጥመጣ እንደነበረችው ነች ” አለ።ቀና ብዬ ታየው ፈገግ አለ ኧረ አፈር ያስበላህ በምዬ ሞት ስንት ፊታቸው ጠቁሮ ፈገግ ቲሉ ልብ የሚበረግዱ የጥቁር ቆንጆዎይ በሞሉባት ሀገር ትትስቅ እንኳን የማያምርብህ ሻንቅላ አንተ ትፈጠር።
ደሞ አፉን ሞልቶ አዲስ አበባ አምስት አመት ኖረይ ቲል አያፍርም እንዴ ቆይ አዲስ አበባ የትዬ ቤት ነው እንዴ? እኔ እንግዲህ ተመጣሁ ተትዬ ቤት እና ተትዬ ፊት ውጪ ምን አየሁና።
የትዬ ስልክ ጠራ። እትዬ ሃሎ እያሉ ወደ ደጅ እንደወጡ ሻንቆ ተተቀመጠበት ሆኖ ወደ እኔ ጎንበስ ቲል በድንጋጤ ልቤ የማማይ መሰለይ።
“ስሚ እንጂ ቆንጆ ወንድ ታውቂያለሽ እንዴ?” አለይ።
መጠየቁስ ጌታው እንዴት ነው ማላቅ !ብዙ አውቃለሁ እይ ምን ማለቶት ነው? ሀገሬ ወንድ ተቸግራ ታውቃለይ ? ታሉስ የወንዶይ ሃብታም ነይ እይ። ያውም የቤት ውስጥ ወንድ ታይሆን እወንዶቹ ታሉበት እጦር ሜዳው ወንድነታቸውን ያሳዩ ስንት ዥግና ወንዶይ አውቃለሁ ትለው… ጥያቄው ምን እንደሆነ ታይገባኝ ቀርቶ ትለመሰለው ሻንቆ ሳቁን ለቀቀው።
ምናባቱ ከጅሎ ይህን ጥያቄ እንደጠየቀይ ታስበው ቢያስደነግጠይም እንዳልገባይ መምሰሉን ቀጠልሁበትና..
ጌታው ለምን ይስቃሉ የምሬን እኮ ነው ትለው ሳቁ ባሰበት።አያ ጅሎ የተናገርሁት ቅኔ እንኳን ታይገባዎት ትለ አዲስ አበባ እና ትለ ገጠር ልጅ ያወራሉ እርሶስ ተወዴት ይሆኑ ? የሰው ልዥ ብልህ አልያም ፉዞ ብሎ ለመፈርጅ ጭንቅላቱ ታላደገ የትስ ቢያድግ ምን ዋጋ አለው።
ጣራ ጣራውን እያየ ቲያስካካ እጎኑ ላይ የሻጠውን ሽጉጥ ተመለከትሁት መዘሽ በከፈተው አፉ ….
ይቀጥላል
4 Comments
ወደነዋል P 32
ወደነዋል p32
P32 ይቀጥል
P32