የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ነበር የተማሪዎቼ የንድፍ ስራ በሙሉ አረንጓዴ…ቢጫ…ቀይ መሆን የጀመረው። የሆነ የቪላ ንድፍ ከመስራታቸው በፊት ሀሳባቸውን በቅርፃ ቅርፅ እንዲያስረዱ ቀለል ያለ ስራ እንሰጣቸዋለን። ያው ያኔ የነበረው መንፈስ ከእጩ አርክቴክትነታቸው በልጦባቸው ቢሮ ውስጥ የሚከመረው ነገር በሙሉ አንድ አይነት ሆኖ አረፈው።መደመር!!!
ብቻ ጊዜው እየሄደ መጣና ነገሮች ተረጋግተው ወደተለመደው የምህንድስና ትምህርት ተመለሱልኝ። በየጊዜው ቦግ እልም የሚለው ግጭት የሩቅ ዜና ነበር። እንደ አንድ ተራ ዜጋ ሀዘን ቢሰማኝም የጉዳዩ ክብደት ይገለጥልኝ የጀመረው ሰነባብቶ ነው። በመቀሌ የነበረው ጦርነት ሰሞን የተወሰኑ ተማሪዎቼ ክፍል ውስጥ መታየት አቆሙ። መልእክቶች ከዚህም ከዚያም “እከሌ እኮ ቤተሰቦቹ ጋር መቀሌ ሄዶ ነው ፋይናል ያመለጠው…ስልክ አይሰራም”…ትንሽ ቆይቶ ወላጆች ትምህርት ከተጀመረ በኋላ ልጆቻቸውን ከክፍለሀገር ዩንቨርሲቲ አስቀርተው እኛ ጋር ማስመዝገብ በረከተ።
“የቀበሌ መታወቂያህ ባለ ብሄሩ ነው አዲሱ?” የሚል የሰቀቀን ጥያቄ በረከተ። ቀስ እያለ “ምሁር” የምላቸው አንዳንድ ወዳጆቼ “እኔ በብሄሬ ምክኒያት ተገፍቻለሁ። አንቺ የማነሽ? ወገንሽን ምረጪ!” አይነት መልእክት ተላለፈልኝ። ለእያንዳንዱ አገልግሎት ከፍዬና ለኑሮ ተባጥሼ በምኖርባት አዲስአበባ የኢኮኖሚ በደል አድርሰሻል ድርሻዬን በልተሻል የሚል አስተያየት ሰማሁ። ጉድ የሚያስብለኝ ይህ ነው! ከትምህርት ቤት ተመርቄ ስወጣ እኮ አለ አንድ ቦርሳ እና የድሀ እውቀቴ ውጪ ምንም አልነበረኝም። ዛሬም እኮ እሷን መንዝሬ ነው በልቼ የማድረው? አይደለም አገሬ ላይ በስደት ብኖር እንኳን የማላጣውን ነገር ማግኘቴ እንዴት ከወንጀል ይቆጠራል?
ይኸው ሰሞኑን ደግሞ ጭፍጨፋውም ማሳደዱም ወደመዲናዋ እየቀረበ ነው። በሁለት መቶ ኪሎሜትር እና ባነሰ ርቀት ውስጥ ሰው ይበለታል።አዎ ነፍስ ናትና የኔ ስትሆን ደግሞ ታሳሳኛለች። ከሞላ ጎደል ሁላችንም የራስ ነገር ሲሆን ሰቀቀናችን ይጨምራል። አንዳንዴ ድንጋይ ላይ የተቀመጡ ፀጉረልውጥ ወጣቶች “ውጪ…ልን” በሚል አይን ያዩኛል። አስባለሁ “የትኛቸው ይሆኑ ገጀራ ይዘው ቤቴን የሚያንኳኩት? የትኛቸው ይሆኑ የሚምሩኝ? ወዴት እሄዳለሁ?እዚሁ ተወልጄ አድጌ ምን ሊውጠኝ ነው?”
አላውቅም…
ቀዳማዊት እመቤቷ ግን የት ጠፍተው ነው?
እየተቆመረ ያለው ቁማር መሀል ማስያዣ ሆነው ይሆን?
አላውቅም…