Tidarfelagi.com

ዕውቀት ይቅደም

” . . . ዕውቀት ይቅደም ነው ያልኩት። ያውም ሰፊ ዕውቀት።

ከአትኩሮት ጠባብነት እንውጣ ማለቴ ነው። ከደቃቃዊነት (Minimalism) ወይም አሹራዊነት (ከአስሩ አንዱን ብቻ ማየት) መሸሽ ነው።
በሌሎች ሃገሮች እዚህ ‘ቀይ ሌሊት’ ዐይነት ስራ ከመድረሳቸው በፊት ታላላቅ ስራዎች ተደጋግመው ተሰርተዋል። ድልድዩ አልተገነባም።
ለምሳሌ ስለ ቅኔ ብዙ እናወራለን ግን ስለ ቅኔና ስለ ግጥም የተጻፉ የጥናት ነገሮች አሳየኝ። አባባሌ ገባህ?
በግዕዝ ብዙ አቀኛኘት እንዳለ እንሰማለን እነዛን ወደ አማርኛ አሻገረናል? ምንስ ይመስላሉ?
ትልቅ ታሪክ አለን ይባላል። እንደዚያ የሚል ሕዝብና ምሁር በተክለጻዲቅ መኩሪያ ሁለት ሶስት መጽሀፎች ብቻ አይቆምም።
ዕውቀቱ የለም። ወይም ይሄ ዕውቀት የተባለው ነገር ማብራሪያ ሊሰሩልን ባልቻሉ ጅምላ አውሪዎች ቁጥጥር ስር ነው።

ስዕል ቢያንስ ከፅሁፍ የተሻለ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ሰዐሊዎች ድልድዩን እየሰሩ ነው። ዘሪሁን፡ እስክንድር ድልድይ ሰሪዎች ናቸው። ከሌሎችም ጋር ሆነው አዲስ ፓራዳይም (የአመለካከት ዕቅድ) እያበጁ ነው። ስነ-ፅሁፍ ግን የለንም።
ምናልባት ዳኛቸው? ምናልባት ጸጋዬ።
በአማርኛ ተጽፎ በእንግሊዝኛ ሂስ የሚሰጥበት ዓለም እኮ ነው ያለነው።

ንቅናቄ የለንም። ደብዛዛ ነገር ነው። ያሉትም ስለፍልስፍናቸው፡ ስለ ቴክኒካቸው ሳይነግሩን፡ ሳያስተምሩን እንዳያልፉ ነው የምፈራው። ስለዚህ ለእኔ ‘ቀይ ሌሊት’ ጋሪ ነው ከፈረሱ የቀደመ።
በማሕበራዊ የድርጊት ዓለም ውስጥ ተስተካካዩ ምሳሌ የተማሪዎች ንቅናቄ ይመስለኛል። ቀይ ሌሊት የተማሪ ንቅናቄ በጋለበት ሰሞን መጻፉ የመመሳሰሉ ምልክት ይሆን?
የአገሪቷን ሕብረተሰብ የምትለውጠው ‘ጭቆና’ በሚል ካልተጠናና ካልተብራራ ፅንሰ ሐሳብ ወይም ኮንሴፕት ተነስተህ አይደለም። እዚህ ፕላኔት ላይ ጭቆና የሌለበት ቦታ የለም። የበለስ በይዎች ዝርያ ነን። ግን ያለህበትን ማወቅ አለብህ።
ምንድን ነው ጭቆና? ኋላ ቀርነትስ?
ምን ዓይነት ባህል አለን?
ጠላታችን ማነው? የጠላታችን ጠባይ ምን ዓይነት ነው?
ከዚህስ ጋር ተያይዞ የመንግስታችን ጠባይ ምን መምሰል አለበት?
ቋንቋችንስ? ቋንቋችን ውስጥ ምን የተደረገ ነገር አለ?
የውስጣችን ባሕል ሲነርጂ ምን ይመስላል? የባህል ውርሰት ጥናቶች አሉ ወይ?
ከውጭው ዓለም ጋር የምንቀራረብበት ሊቃዊ መንገድ ምንድን ነው? ወዘተረፈ…..
ብዙ ጥያቄዎች አልተመለሱም፤ በጥናት ማለቴ ነው።
***
አቴሜቴ ሎሚ ሽታ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *