እንደ ጊዜው መክፋት
እንደ ግፉ መስፋት
እንዳገሩ ክስመት
እንዳገሬው ጥመት
እንደሰው ጭካኔ፥እንደ ልቡ ፍሬ
ታምር ነው መትረፍሽ፥ ታምር ነው መኖሬ።
የበጎ ሰው ሀሳብ፥ ሲካድ እለት በእለት
ጉድጓድ ተምሶለት፥ ሰብእና ሲቀበር
በዚህ ዓለም መኖር፥አያስመኝም ነበር ።
ምድሩ ሳር ቅጠሉ፥ በስጋት ተሞልቶ
የማለዳው ሰማይ፥ እንዳንቀልባ ቀልቶ
ታረደ
ነደደ
ከዘብጥያ ወጥቶ
ዘብጥያ ወረደ
የሚል ዜና ብቻ ፥ አየሩን ሲሞላው
ሰው በገዛ ጥላው ፥
በርግጎ ሲሸበር
በዚህ ምድር መኖር፥ አያስመኝም ነበር ፤
አዎ
ለጊዜውም ቢሆን ግፍ ያደነዝዛል
በደል ያስተክዛል
ጊዜም ጠብን ሽሮ፥ ወደ ፊት ይጓዛል
በልብ ሰሌዳ ላይ፤ ቂም ይደበዝዛል
በነገ ያመነ
ልጁን ቀብሮ መጥቶ ፥ ሚስቱን ያስረግዛል።
ይቅርታና ምህረት
ፍቅርና ህብረት
ከግፍ ጋር ፍልሚያቸው፥ ቢሆን የሞት ሽረት
ዳገት ይወጣሉ፥ በንጥፍጣፊ አቅም
የመኖር ፍላጎት
ዘመም ይላል እንጂ ፥ተገርስሶ አይወድቅም።
( አዳምኤል )
One Comment
እንደሰው ጭካኔ እንደልቡ ፍሬ፡
ታምር ነው መትረፍሽ ታምር ነው መኖሬ!!! የበጎ ሰው ሃሳብ ሲካድ እለትበእለት…!!!!!!!