Tidarfelagi.com

የመብራት የመጥፋት ትዝታ፤ከባለፈው የቀጠለ

ከጥቂት አመት በፊት የረር በር እኖር ነበር፤አንድ ቀን መብራት በጊዜ ጠፋ፤እስከ እኩሌሊት ድረስ ስላልመጣ ተስፋቆርጠን ተኛን፤ ዘጠኝ ሰአት ላይ ሚስቴ ቀሰቀሰችኝና ወደ ምኝታቤቱ መስኮት ጠቆመችኝ፤ የሆነ ግዙፍ እጅ ጥላ መስኮቱን ሲዳብስ ይታየኛል፤

“ሌባ ነው?” አልኩዋት፤

ራሱዋን ባዎንታ ወዘወዘች፤

“መስኮቱን ምን እያረገው ነው?” አልሁ እምለው ጠፍቶኝ፤”

“እየወለወለው” አለችኝ በብሽቀት በሹፈት፤

( እኔ ግን እንዲህ አይነት ደደብ ጥያቄ እንዴት እጠይቃለሁ?)

ወድያው ኡኡኡ ማለት ጀመረች፤ መጀመርያ እማደርገው ነገር ጨንቆኝ ተገትሬ ቀረሁ፤ሱሪየን ለመታጠቅ ስሞክር የግሬን ማስገቢያ ሶስት ጊዜ ሳትኩት፤ ሚስቴ “ ጋሽ ኤባ! እትየ አምሳለ! አቶ ዮፍታሄ !ኡኡ ድረሱልን! ሌባ ሌባ ትላለች!” እኔም የበኩሌን ለማድረግ ሞከርኩ ፤ ጉሮሮየ ትንሽ ተግደረደረና በመጮህና በመፎከር መሀል የሆነ ነገር ለጎረቤት አስተላለፈ፤

(አቤት ይሄኔ አባቴ ቢሆን ኖሮ! ድሮ ልጅ እያለሁ፤ አባቴ ሌባ የሳሎኑን በራችንን ሲሰረስር ከሰማ፤ ብንን ይልና እናቴን “ እሽሽሽ ! አደራ ጮሀሽ እግዜር በስንት መከራ የመጣልኝን ቀማኛ እንዳታስመልጭብኝ” ይላታል፤ከዚያ በጉዋሮ በር ሾከክ ብሎ ይወጣና ኮቴውን አጥፍቶ፤ ከሌባው ጀርባ መጥቶ በሾኬ መቶ ይጥለዋል ፤ከዚያ እኛን ከጣፋጭ እንቅልፋችን ቀስቅሶ ይዞን ይወጣና ፤” አያችሁ ልጆች? ተግታችሁ ካላጠናችሁ እንደዚህ ሌባ ትሆናችሁ” በማለት ተግሳፅና ምክር ይለቅብናል፤ ሌባው ፌይንት ካደረገበት ሲነቃ አባየ ሌባውን ቁልቁል በንቀት እያየው” እናስ አንት ሞላጫ! ነገ ባደባባይ ድንጋይ ተሸክመህ ይቅርታ ትጠይቀኛለህ ፤ወይስ አሁን ድንጋዩን ደረትህ ላይ እንድፈልጥ ትፈቅድልኛለህ?” ይለዋል! አይ አባየ! አይ ቆራጥ!

አሁን ወደ እኔ ስመለስ በፉከራና በጩከት መካከል የሆነ ድምፅ አወጣሁ፤ሚስቴ ግን እሪሪሪታውን በተለያየ ቅኝት እየለቀቀችው ነው! ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ግቢያችን በፈጥኖ ደራሽ ጎረቤት ተወረረ፤ሌባው በበጀት እጥረት ምክንያት የሰርከስ ኢትዮጵያ የተቀነሰ ሳይሆን አይቀርም፤ በልብስ ማጠቢያ ጎማ ላይ ነጥሮ፤ ግንቡን በቅልጥፍና ዘሎ አቀጣጥኖታል!

ከሰፈራችን ትጥቅ የሌለኝ እኔ ብቻ መሆኔን ያንቀን ተረዳሁት፤ እነፌሮ እነ ከዘራ ሳይቆጠሩ በግቢያችን ውስጥ ሁለት ክላሽ አንድ ኡዚ ታየ፤ ጎረምሶች ትከሻየን እየዳበሱ አበረታቱኝ፤ሴቶች ሚስቴን አፅናኑዋት፤
የማረጋጋቱ ስራ በጥሩ ሁኔታ እንደቀጠለ አንድ ነገር ተፈጠረ ፤ ጋሽ ኤባ ሳቃቸውን በጋቢያቸው ለማፈን እየሞከሩ “ለመሆኑን እሱን ምን ልታረገው ነው የያዝከው?” አሉኝ፤
አይኔ ወደ ቀኝ እጄ ላክሁት፤ለካ በድንጋጤ፤ ትራሴን ይዤው ወጥቻለሁ፤

የግራ ጎረቤታችን ወይዘሮ አምሳለች እንዲ ሲሉ ሰማሁዋቸው፤

“ ሌባውን አፍኖ ሊገልበት ይሆናላ እንግዲህ”

One Comment

  • ሰለሞን መኮንን commented on June 7, 2019 Reply

    1

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *