ከዕለታት አንድ ቀን ‘ጣይቱ’ የተባሉ እተጌ እዛች ፍልውሃ የምትባለው የምትጤስ ቦታ፣ እዛች እርጥብ ፊንፊኔ ገላቸውን ተጣጥበው ጨርሰው፣ ከተቀመጡበት በርጩማ ብድግ ሲሉ፣ እንደ ደንግ የምታበራ የሕልም እንቁላላቸው የምትሞቅ ግልገል ኩሬ ውስጥ ወደቀች፡፡ ከዛም ወደ ተሰራላቸው ማረፊያ ጎጆ አቀበቱን ሲያዘግሙ፣ ስሟ የተጠራ ከተማ የመቆርቆር ምኞታቸው በሚያልፉበት ጎዳና ላይ ከአንደበታቸውና ከረጠበ ጉንጉናቸው ተንጠባጠበ፡፡ ባለቤታቸው ንጉሠ ነገሥት ሚኒሊክን ጨምሮ ሕዝቦች ያን ከፍል ውሐ ጉም እስከ ባዕታ ወይራዎች ድረስ የተዘራውን የእመቤታቸውን ምኞት አተኩረው እንደ ጥሬ ለቀሙ (ምንም እኳን በንግርት ባላቸው እንጦጦ ላይ የታፈረ መንግስት እንዲያቆሙ ንግርት አለ ቢልም)፡፡ ቅጠል በልቶ ከተነበየ ባሕታዊና አውቃለሁ ባይ የአምደ ፅዮን ዘመን ደብተራ ይልቅ ጎርጎራ ከተማ በጣና ዳር በመረጋጋት የሰለጠነ የንግሥት ጣይቱ ድምቡሼ ገላ ትንቢትን አሸነፈ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ምኒሊክ እንጦጦ ማሪያም ግቢ ጉባኤ ጠርተው መኳንንቶቻቸውን እንዲህ አሉ፡
“አዲስ አባን እንካችሁ፡፡ ተጠራርታችሁ ሙሏት”
እነሱም እንደ ተባሉት ሠራዊቶቻቸውን እየመሩ ፍል ውሃ ዙሪያ ሳርና ጭቃ ላይ እንደ ጨርቅ ተጣፉ፤ እንደ ድንጋይ ተኮለኮሉ፡ ሸጎሌ፣ አባ ኮራን፣ ጉለሌ፣ ጎላ፣ ተረት ሰፈር፣ ሠራተኛ ሰፈር፣ አራዳ…… እንዲያ እንዲያ እያለ በጅረት እና በወንዝ የተሸረሸረች፣ አፈርና ሳር የነበረችው የፊንፊኔ ሜዳ በሰውና በጎጆ፣ በሰንሰልና በባሕር ዛፍ ሞላች፡፡ ዘመናዊ ለመሆን ማሽቃበጥ ስትጀምር በ1928 ጣሊያን ገባና በሲሚንቶ፣ በዘረኛነት፣ በአስፋልት…… ይሄንንም እንዲያዳምቁ ጦርነት የበተናቸውን ወይዛዝርት ሰብስቦና አደፋፍሮ በመለኮ (እዝራ እንዳለው) አጎለበታት፡፡ በ1933 አ.ም. ላይ ትቷት ሲሄድ የምንወደውን፣ የሚቀርበንንና የምንችልበትን ጠበቅን፡ ጥቂት ትምህርት ቤቶችን፣ አልሞት ያለ የአስፋልት መንገዱን፣ ለገሃርን፣ ፖፖላሬን፣ ካዛንቺስን፣ ፒያሳን፣ መርካቶን አረቄና ሽርሙጥናን (ልጅን ሲወዱ ከነንፍጡ)፡፡
ያኔ ይሄ ሁሉ ሲሆን ሽሮሜዳ፡ በእግር መንገዶች የተሸነሸኑ አረንጓዴ አራዳ ሜዳዎች የገነኑባት፤ ጥቁርና ቀይ አፈራቸው በዝናብና በጎርፍ የፈረሱ ተረተሮች አረሆ የተቀረፁባት፣ በጋ በጋ የሚደርቁ ጭቃማ ጅረቶች የሚሰርቡባት፣ ሚዳቋዎች ከተራራው እየዘለሉ መጥተው እየዘለሉ የሚሸሿት፣ በአጋም፣ በቀጋ፣ በቁጥቋጦና በፅድ ደኖች መሃል አሾልከው የሚያዩ ጎጆዎች የፈሉባት፣ ዝግባ ዛፍ ስር ያደፈጡ መንገደኛ መቀበያ ኮሳሳ ማደሪያዎች የተጎለቱባት፣ የቄስ የደብተራና የገበሬ ቅልሳቶች ያፈጠጡባት፣ የገግና የበሬ ነጋዴዎች ጉሮኖዎች የተነቀሱባት፣ ልብሳቸውን ሳር ላይ የሚያሰጡ ወይዘሮዎች የሚያንጎራጉሩባት፣ ጠዋት ማታ የሚንጋጋ ጅብ እዚህና እዚያ በነጭ ኩሱ የነቀሳት ቦታ ነበረች፡፡
እኔም ነጋ ጠባ ባሳፈፈ የእንጨት ጭስና የባሕር ዛፍ ድምድማት ተከልሎ ይኑር አይኑር በማይታወቀው የአዲስ አባ ማዕከልና በዝናብ እየታጠበ፣ የሌሊት ዝምታው ቋጠሮ አሁንም አሁንም በጅብ እሙኝታ፣ በውሾች የሌሊት ሃዝ ሃዝ፣ በሚፈታው የእንጦጦ ተራራ መሃል፣ ከኋለኛው ቀርቤ ከፊተኛው ዕርቄ ተወለድኩ፡፡ የከተማችን ቀያሾች ‘መዲባ’ ይሏታል፡፡ በመዲናና በባላገር መሃል ናችሁ ሲሉን፡፡ እየሰደቡን ይሆን እየመደቡን ይህቺ ማርያም ታውቃለች፡፡
ሽሮሜዳ ‘ሽሮሜዳ’ የተባለችው የአረጋሽ ባል ጋሼ ሰይፉ ሲያወራ እንደሰማሁት እዚህ አካባቢ በድሮ በድሮ ጊዜ ሰፈሩን አፈሩን ሽሮ መስሎአቸው ወጥ ሰርተው በልተውታል ተብሎ ነው አሉ፡፡ ስለ የድንጋይ ዳቦ ዘመን ከተወራ ስለ የአፈር ሽሮ ዘመን አይቻልም?
ሽሮን (ስናቆላምጣት) የአዲስአባ ፕላን አውጪዎች ከሚያዳሉላቸው ቦሌና አሮጌው አይሮፕላን ማረፊያ ውበቷ ይበልጣል፡፡ የመስከረም አረንጓዴና ቢጫነቷን? በየመንገዶች ግራና ቀኝ ከእንጦጦ የሚወርደውን ወርቅማ ውሃዋን…… እንጦጦ ወጥተን በላስቲክ ኮሮጆ ሰብስበን የምናመጣቸውን አጋምና ቀጋዋን ማን ይስተካከላታል?
ሽሮሜዳ እያደገች ብዙ ሰዎች ሊኖሩባትና ሊሰሩባት መጡ፡፡ የአልማዝ ጉርጉሱም ሆቴልና ተራራ ካፊቴሪያ ተከፈቱ፡፡ ግራና ቀኝ በየመንገዱ ዳርና ዳር ቡና፣ ጠላና አረቄ ቤቶች ተደረደሩ፡፡ ጥቂት ልብስ ሰፊዎችና የልብስ ሱቆች እዛ እዛ ተተከሉ፣ የሚያምር አጂፕ ነዳጅ ማደያ ከተራራ ሆቴል ዝቅ ብሎ ተከፈተ፡፡ ጫማ ሰሪዎች ትናንሽ መጠለያቸው ውስጥ መዶሻቸውን ይዘው ተቀመጡ፡፡ በዚች ጥቁር ሰረሰር በመሰለች አስፋልት መንገዳችን ጠርዝ ሸንኮራ ሻጩ ዋሕድ እየተጎማለለ መዘየር ጀመረ፡፡
የዚህ ሰፈር ሰዎች ሕብስት አያምራቸው፣
አጅሬ ሸንኮራ ገብቶ ከቤታቸው!!
ቅልብጭ ባለችው ለግላጋ የመንደራችን ካርታ ላይ ሰካራም በረታ፡፡ እኔም እንደ አካባቢዬና እንደ ከባቢዬ ብዙ አለማዊ ዕውቀት ተማርኩ፡፡ ጊዜ አልወሰደብኝም በጉጉቴ ስፋትና በቀልቃላነቴ ጥልቀት ከከተማውም ከገጠሩም የደባለቀ የመዲባ ዜጋ፣ ደህና ዲቃላ ሆንኩ፡፡
መረቅ፣ ገጽ 11 – 13
One Comment
ይህ የነተበ እና የነፈዘ አለም ያንተ እና የመሰሎችህ የብዕር አረፋ ባይኖር ማን ፅዓዳ ያረገው ነበረ እጅህን ቁርጥማት አይንካው አዳምዬ።