Tidarfelagi.com

የተሳሳተ

ከምኡዝ ጋራ ከረጅም ጊዜ በሁዋላ ተገናኘን፥ “ ከመንገድ ዳር ካለ አንድ ካፌ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን አቧራና ቡና እየጠጣን አላፊ አግዳሚውን እያየን እናወራለን፥ ድንገት አንዲት ሴት ብቅ አለችና ወደ ምኡዝ እያየች “ አንተ አለህ?” ብላ ባድናቆት ጮኸች፤ ሁለት እጆቿን በሰፊው ዘርግታ እቅፍፍፍፍፍ አደረገችው፤ ቀጥላ እኔንም እቅፍ ታደርገኛለች ብየ ተስፋ አደረግሁ ፥
ከእቅፉ ወጣችና እንደገና እጅጌዋን እስከ ክርኗ ሰብስባ ባዲስ ጉልበት ተጠመጠመችበት፤ ወረፋው እስኪደርሰኝ ከኪሴ ዶዶራንት አውጥቼ ብብቴ ላይ ነፋሁ፤ አሁንም እንደገና ተቃቀፉ፤ ስራ ከምፈታ ብየ ከግራ ብብቴ ላይ በላብና በዶዶራንት የፋፉ ሁለት የጸጉር ዘለላዎችን ነቀልሁ፤ በመጨረሻ ፈገግታየን እንደ ደጋን ወጥሬ፥ እጄን እንደ በረኛ ዘርግቼ ተጠጋሁዋት። ልጂቱ ግን ጸጉር የከበደውን ራሷን ዘንበል አድርጋ ሰላምታ አቀረበችልኝና ሄደች! በቴስታ ብትነቀንቀኝ ራሱ እንደዚያ አያመኝም! ላለማፈር በዙርያየ ባለው ማህበረሰብ ፊት የምንጠራራ መስየ ለመታየት ሞከርኩ፥
“የት ነው የምንተዋወቁት?” አልኩት
“ከምታውቀው ሰው ጋራ ተምታትቸባት መሰለኝ” አለኝ፥
“እንደ ሀረግ እሬሳ የተጠመጠመችብህ ሳታውቅህ ነው?
“ምን ታረገዋለህ ፥ እድለኛ ከሆንህ ለሌላው የተላከ እቅፍ ይደርስሀል፥ እድለቢስ ከሆንህ ደግሞ ለሌላው የተወረወረ ድንጋይ ይፈነክትሀል! እድል ነው”
ከጥቂት ቀናት በፊት የደረሰብኝ ነገር ትዝ አለኝ፥
የሆነ ቦታ ደወልኩ፥ የደወልኩት ስልክ አይነሳም፤
“ውድ አቤል! ከአሜሪካ የተላከልህ እቃ ስላለ መልሰህ ደውልልኝ” የሚል መልክት ጽፌ ሰደድሁ፤
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ስልኩ ተደወለልኝ።
“ቁጥር ተሳስተሀል” የሚል የሴት ደምዽ መጣ፤
ይቅርታ ጠይቄ ስልኩን ዘጋሁት፤ ጥቂት ቆየቸ ግን መልሼ ደወልኩ፤
“ሄሎ “
“ተሳስተሀል አልሁህኮ” አለቺኝ ሴቲቱ፥
“ገባኝ”
“ከገባህ ምን አስደወለህ?”
“ምናልባት ለምክንያት የሆናል የተሳሳትሁት የኔ እመቤት! ደሞ ማን ያውቃል፥ የተሳሳተ ቁጥር የተሳካ ትዳር መሰረት ሊሆን ይችላል”
“ተው ባክህ”
“ቁንጅናየን ይንሳኝ!”
“ሆሆ ። ለመሆኑ ማን ልበል? “
“በውቄ እባላለሁ”
“ለማቆመጥ እስኪያበቃኝ ሙሉ ስምህን ብታስተዋውቀኝ”
“በእውቀቱ “
“እሺ አቶ በወቅቱ ፤ እስቲ ስለ ራስህ ንገረኝ”
“መልኬ በጠይም እና በቀይ መሀል ነው-ቀይም!”
“ቁመትህ? ስንት ሜትር ነው?”
“እሱን በሚሊሜትር ብንነጋገር ደስ ይለኛል የኔ እመቤት”
“ሄሎ፤ የስልኩ ድምጽ ይቆራረጣል ፥ የት ሆነህ ነው?”
“ቤንዚን እያስቀዳሁ ነው”
“ለመኪናህ?”
“በምን እድሌ! ለፋኖሴ ነው እንጂ”
የተራዘመ ዝምታ፥
“ስምሽ ማን ነው” አልኩዋት በመጨረሻ፥
“ጄሪ”
“ለማቆላመጥ እስከደርስ ሙሉ ስምሽን ብትነግሪኝ”
“ማን ይመስልሀል”
“ጀሪካን?”
ስልኩ ተዘጋ።
ምን አናደዳት? ባሁኑ ጊዜ በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት ውስጥ ከጀሪካን የተሻለ ፋይዳ ያለው ነገር እንደሌለ ባይይገለጥላት ይሆናል፥
መልሼ ለመደወል ተሰናዳሁ፤

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *