Tidarfelagi.com

የተካደ ትውልድ

የተካደ ትውልድ
አይዞህ ባይ የሌለው
ታዳጊ የሌለው
ወይ ጠባቂ መላክ፥ ወይ አበጀ በለው
ደርሶ ከቀንበሩ ፥የማይገላግለው፤

የተካደ ትውልድ
አብዝቶ የጾመ፥ ተግቶ የጸለየ
ጥቂት መና ሳይሆን፥ ጥይት ሲዘንብ ያየ
እድሜ ይፍታህ ተብሎ፥ የተወለደ ለት
አምባሩ ካቴና፥ ማተቡ ሰንሰለት፤
ምቾትን የማያውቅ፥ ረፍት የተቀማ
አልጋው ያጋም እሾህ፥ ምኝታው የሳማ፤

የተካደ ትውልድ
ሞቶ እንኳን ሬሳው፥ አይላላለት ቀንበር
በዘብ እጅ ተገድሎ ፥ በሹም የሚቀበር
ከጡት አስጥል በላይ፥ ኑሮ የመረረው
እንዳይሄድ ጎዳናው ፥ የተደናገረው
ድል ያልሰመረለት ፥ትግል ሳይቸግረው።

የተካደ ትውልድ
በስጋ በነፍሱ
በቀልቡ በገላው
ከቶ ምንድን ይሆን?
ምንድን ይሆን መላው?

(የማለዳ ድባብ፥ 28)

2 Comments

  • adane ewnetu commented on December 7, 2022 Reply

    በወቄ እረዥም ዕድሜ ከሰላምና ከጤና ጋር

  • yonasbirhanu commented on June 6, 2023 Reply

    በእውነት ግሩም ነው!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *