ባየኋቸው ቁጥር ግርርም ከሚሉኝ ታሪካዊ ፎቶዎች አንዱን ላካፍልዎት፡፡ በ1935 የተነሣው ይህ ፎቶው የተገኘው ባሶሼትድ ፕሬስ መዝገብ ውስጥ ነው፡፡ በፎቶው ላይ ለጊዜው ስሙን ያልደረስኩበት ሠዓሊ የግርማዊት እቴጌ መነን እና የአዶልፍ ሂትለርን ሥዕል ሲሸጥ ይታያል፡፡ በፎቶው ጀርባ ላይ እንደ ተገለጸው ከሆነ፤የጀርመኑ አምባገነን ምሥል አምስት ብር ለገበያ ሲቀርብ የእቴጌ ምስል ግን በቅናሽ ሦስት ብር ቀርቧል፡፡ ያም ሆኖ ሸማቹ አዲስ አበቤ የእቴጌን ምሥል ቸል ብሎ የሂትለርን ምሥል ለመግዛት ቋምጧል፡፡
ጉድ ነው!
የሂትለር ፊት እንዴት የእቴጌን ፊት የሚያስንቅ ዋጋ አወጣ?
ፎቶ አንሺው ስለ ሥእሉ መነሻ የሚነግረን ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ግምትዎን እንዲሰጡ እየጋበዝኩ ግምቴን ላስቀድም፡፡
የሙሶሎኒ ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ስታውጅ ያለም ኃያላን መንግሥታት ኢትዮጵያን ዓይንሽ ላፈር ብለዋት ነበር፡፡ የቀ.ኃ.ሥ አማካሪ የነበረው ዮሀንሥ ስፔንሰር እንደ ነገረን ፤ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ጠመንጃ የመጸወተች ብቸኛ ኣገር ብትኖር በሂትለር የምትመራዋ ጀርመን ነበረች፡፡: ሠዓሊው ላገሩ የተደረገውን ውለታ ለመዘከር Heil Hitler! እያለ ይሆን?
የፎቶው ትንተና የተመሠረተው በሚከተለው ታሪካዊ ሐቅ ነው፡፡” In 1959,Haile Selase told an astonished French Newspaperman that Germany had provided Ethiopia with the most assistance during the crisis .In early 1935,persistent rumors to that effect were regularly denied by Germany ,although they were credible in terms of the longstanding Nazi-Fascist antagonism over Austria.(Harold Marcus .Haile Seilase 1)