Tidarfelagi.com

የዘገየው ዘማች

ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተገረበ

ረጂሙ መስታውት ፊት ቆሜ ዘናጭ ሱፌን ለበስኩ። ክራቫት ማሰሩ ላይ ግን አልተሳካልኝም። የክራቫቴ ራስ ባንድ ጎን ተድቦልቡሎ የቡዳ መዳኒት መስሏል።

ቁርሴን በልቼ በዳግማዊ ምኒልክ ሀውልት ስር የማስቀምጠውን አበባ ለመግዛት ወጣሁ። ገና አፋልቱ ላይ ልደርስ ስል አንዱ ብቅ አለና:-

“በውቄ አድናቂህ ነኝ!”

“በጣም አመሰግናለሁ” አልሁኝ ፈገግታየን በርግጄ።

“የመጨረሻውን መፅሀፍህን ስንት ኮፒ አሳተምህ?”

“አስር ሺ”

“የማትፈልገው አስር ብር ይኖርሃል?”

ፈገግታየ ድራሹ ጠፋ።

” አትፍረድብኝ መሮኝ ነው!! አንገፍግፎኝ ነው” አለኝ ፈላጩ ራሱን እያከከ።

“ኑሮ ይህን ያህል ካንገፈገፈህ ለምን አንድ ሊትር ናፍጣ ገዝተህ ራስህን አታቃጥልም?”

” አንድ ሊትር ናፍጣ ስንት ነው?”

” አምሳ ብር?”

አምሳ ብር ካለኝ !! ለምን ራሴን አቃጥልለሁ? ”
“አንድ ዙርባ አልቅምም?”

አሳቀኝ ስለተመፅዋችነቱ ሳይሆን ስለኮሜድያንነቱ አስር ብር ሸለምኩት።

” አመሰግናለሁ!! ኢትዮጵያ ሲያልፍላት ውለታህን እከፍላለሁ!!” አለኝ ፈገግ ብሎ።

” ኢትዮጵያ ያልፍላታል ብለህ ታስባለህ?”

” ታድያስ መንግስት ደብቆት ነው እንጂ በምሥራቅ ኢትዮጵያ : ለቀጣይ ሁለት መቶ አመት የሚቆይ ጋዝ ተገኝቷል”

” ምን አይነት ጋዝ?”

” አስለቃሽ ጋዝ”

በድጋሜ ስላሳቀኝ ሃያ ብር ጨመርኩለት።

…አበባ መሸጫው እስክደርስ : አባቴ ስለ አድዋ የነገረኝን ያልተሰማ ታሪክ ላጫውታችሁ።

🏹🏹🏹🏹🏹🏹🏹

ባጤ ምኒልክ ዘመን ፈጠነ ሞገሴ የተባለ ዝነኛ ሽፍታ ማንኩሳ ውስጥ ይኖር ነበር። ያድዋ ብሄራዊ ውትድርና አዋጅ ሲታወጅ ፈጠነ ሞገሴ ዱር ውስጥ ስለነበር ያዋጁ ቃል የደረሰው በጣም ዘግይቶ ነው። ታድያ: ያዋጁን ቃል እንደሰማ ባጭር ይታጠቅና ወደ ጦርሜዳ ብቻውን ይገሰግሳል። ፈጠነ ሞገሴ ቀንና ሌት ተጉዞ አሸንጌ ላይ ሲደርስ ያጤ ምኒልክ ሰራዊት ውጊያውን በድል አጠናቆ ሲመለስ አገኘው።ፈጠነ የንጉሱ ሰራዊት እየፎከረ እየሸለለ ተሰልፎ ሲያልፍ ሲያይ በቅናት ሊያብድ ደረሰ። ወደ አገሩ ሲመለስ ለሚስቱ ምን ሊያወራት ነው? ምን ግዳይ ሊያቀርብላት ነው?! መጀመሪያ የመጣለት ሀሳብ ” ዘመቻው ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት ስላላሳተፈ ጦርነቱ እንዲደገም ግርማዊነትዎን እማፀናለሁ” የሚል ደብዳቤ ለምኒልክ መፃፍ ነበር። ይህ እንደማያዋጣ ገባው።

ሌላ ዘዴ ለማውጠንጠን ከጎዳናው ተዘንጥሎ ባቅራብያው ወደሚገኘው ዱር ገባ። ይህ በእንዲህ እያለ : ከሰራዊቱ ተገንጥሎ ወደ ሁዋላ የቀረ አንድ የመንዝ ዘማች የማረከውን የጥልያን በበቅሎ ላይ አስቀምጦ እየነዳ ሲመጣ ተመለከተው። ይቺን ይወዳል ፈጠነ ሞገሴ!! ፈጠነ ሞገሴ ጠብ አማረው። ግን የጠብ ምክንያት በቀላሉ ስላልመጣለት ተናደደ። ወድያው ግን አንድ ሰበብ ብልጭ አለለት። የመንዙን አርበኛ መንገድ ዘግቶ ” ጌታው!! ፈረንጁን ምርኮኛ በቅሎ ላይ አስቀምጠህ አንተ በእግርህ መሄድህ ምን አስበህ ነው? የጥቁር ዘር ከታች የነጭ ዘር ከላይ ነው ለማለት ፈልገህ ነውን? የድሉን ፍሬ ለማራከስ ፈልገህ ነውን?” ብሎ ነገር ፈለገው። አንዳንድ ሲባባሉ ቆዩና መፋለም ጀመሩ። ፈጠነ ሞገሴ ባረፈ ጉልበት ለተፋለመ ወደረኛው ሊቋቋመው አልቻለም። በዚህ ፍልሚያ የመንዙ ወታደር ለመጀመርያ ጊዜ ሲማረክ : ጣልያኑ ለሁለተኛ ጊዜ ተማረከ”…

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *