Tidarfelagi.com

የዝዋል ድንኩዋን እንዳይሆን

ከጥቂት ወራት በፊት ሃያ ሁለት ማዞርያ ተቀምጠን ለገ ጣፎ ላይ ሲጨስ የተለመለከትን እኔና ብጤዎቼ አሁን ያለውን አንፃራዊ መረጋጋት እንደ ብርቅ ነገር ብንቆጥረው አይፈረድብንም። ያኔ ምንም ማድረግ ምንም ማለም የተሳነን ምስኪኖች ነበርን ። አሁን ከምስኪንነት ወደ ጀግናነት ተሸጋግረናል። “ጀግናነት ማለት ታላቅ ተስፋንና ታላቅ መከራን ባንድ ላይ መሸከም መቻል ማለት ነው” ይላል ኒቸ የተባለ የጀርመን ሊቅ።

ታላቁ ተስፋ የመነጨው በፍጥነት ከተመዘገቡት ሰሞንኛ በጎ ለውጦች ነው። ያም ሆኖ ከታላቁ መከራ ሙሉ በሙሉ አልተገላገልንም። የኑሮ ውድነት ብሶበታል። መብራትና መብላት በፈረቃ ሆኑዋል። ዜጎች በየቦታው እየተፈናቀሉ ነው። በተለይም የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ከኖሩበት ቦታ እየተገፉ ” አገሬ ውስጥ ሆኘ ናፈቀኝ አገሬ” የሚለው እንጉርጎሮ ብሄራዊ መዝሙራቸው አድርገው እንዲወስዱት እየተገደዱ ነው።

ያዲሱ አመራር ፊታውራሪዎች በየመድረኩ የሚያቀርቡት አሰባሳቢ ንግግር የሚመሰገን ነው። ይሁን እንጂ ቅን ሀሳባቸውን ወደ ተግባር የመመንዘር እዳ አለባቸው። እኛንም “ይሄ ነገር ዘላቂ ለውጥ ነው? ወይስ የዝዋል ድንኩዋን ነው ” ከሚል ማመንታት ይታደጉን።

የዝዋል በራሪ ድንኩዋን!

– አንድ ባላገር ቀኑን ሙሉ ገበያ ውስጥ ሲማስን ውሎ ወደ ሰፈሩ ሲመለስ ዝዋል የሚባል ቀየ ይደርሳል። ከሩቅ ጅረት ዳር የተንጣለለ ነጭ ድንኩዋን ይመለከታል። ከፊቱ የሰርግ በረከት ተንጣሎ እንደሚጠብቀው አልተጠራጠረም: ” እሰይ!! ድግሴን በልቼ አንድ ሁለት ዋርማ ጠላ ጠጥቼ ጉዞየን እቀጥላለሁ” ብሎ በማመን ወደ ሲሳዩ አቅጣጫ ጉዞ ጀመረ። ሲሄድ ሲሄድ ውሎ ሲደርስ ያልጠበቀው ነገር ገጠመው። ነጩ ድንኩዋን ከፊቱ ብድግ ብሎ በረረ። ለካስ በቦታው የነበረው ድኩዋን ሳይሆን ሸመላ የተባለ ያሞራ መንጋ ኑሩዋል። ባላገሩ “ወትሮስ በዝዋል ሊሰረግ! ” ብሎ በማማረር በትራፊ ጉልበት ወደ መጣበት ተመለሰ።

እኔና ብጤዎቼ እንደ ደበበ ሰይፉ
“የጣልኩብሽ ተስፋ
እኔን ይዞ ጠፋ” ብለን ከማንጎራጎር የሚታደገን ርምጃ እንጠብቃለን።

አሁን የምናየው ነገር :የዘላቂ ለውጥ መጀመርያ እንጂ የዝዋል በራሪ ድንኩዋን አለመሆኑን አሳዩን።

One Comment

  • Girma commented on July 25, 2018 Reply

    ጉራ ብቻ እንዳይሆን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *