Tidarfelagi.com

የድሮ ዘፈን ላይ የቀረበ አጭር ትንታኔ!

 

የድሮ ዘፈን ነፍሴ ነው ! የድሮ ዘፈን የሆነ ቬጂተርያን ቃና ነበረው:: በጊዜው ያልተዘመረለት የዱር ፍሬ የለም! “ የሾላ ፍሬ ” “ እንኮይ እንኮይ” “ ብርቱካኔ” “ ሸንኮራ” “ ፓፓየ” ነሽ !
“ ተቀጠፈ ሎሚ ተበላ ትርንጎ/ ከሸጋ ልጅ መንደር በስሎ ተንዤርግጎ ! “ የምትለዋን የነዋይን ግጥም ማን ይረሳል? ምን ዋጋ አለው! ከለታት አንድ ቀን ታደሰ አለሙ የሚባል ዘፋኝ ተነስቶ የአማርኛን ዘፈን ስጋ በስጋ አደረገው !

የድሮ ዘፋኞች ከማዝናናት ጎንለጎን ጠቅላላ እውቀት ይለግሱ ነበር ፤ ህዝቡ ስለቤት እና የዱር አራዊት ጠባይ መረጃ እሚያገኘው ከዘፋኞች ነበር ፤ ለምሳሌ፤
“ካላጉረመረመ አይበላም ነብር( ይርጋ ዱባለ) –

“የቁልቁለት መንገድ ለበቅሎ አይመችም” ( ሙሉቀን መለሰ)

“የእባብ ዘለግላጋ የለውም እግር እጅ “ (አለማየሁ እሸቴ )

“ዶሮ ውሃ ጠምቶት ተንጋሎ ይጠጣል” (ንዋይ ደበበ)

“ፍየል ቅጠል እንጂ አትበላም እንጉዳይ” ( ንዋይ ደበበ)

ባጠቃላይ ፤ የድሮ ዘፈን ራሱን የቻለ ናሽናል ጆግራፊ ቻናል ነበር ማለት ይችላል !

በደምሳሳው ሲታይ የድሮ ዘፈን ግጥም ብዙ አይመስጥም! በኔ ግምት ሁለመናው የተዋጣለት የዘፈን ግጥም የተጀመረው በይልማ ገብረአብ ነው ! አሁን ደግሞ የሀብታሙ ቦጋለን፤ የአብርሃም ወልዴንና የኑረዲን ኢሳን ግጥሞች አጣጥማለሁ፤

ከቆዩ ዘፋኞች ውስጥ ግጥም እማይሰምርለት ኢያዩ የሚባል ዘፋኝ ነበር ! የኢትዮጵያ ሬድዮ እግር ኩዋስ ባስተላለፈ ቁጥር ለምን የሱን ዘፈኖች ጆሩዋችን ላይ እንደሚጥዳቸው እስታሁን አይገባኝም !

“ እንስራዋን አዝላ በወገቡዋ ላይ
ውሃ ልትቀዳ መሄዱዋ ነው ወይ ? “
ይላል ኢያዩ::

እረ የለም ! እንስራዋን ውሃ ዋና ልታስተምር እየሄደች ነው 😕

በነጭና ጥቁር ቲቪ ይተላለፉ የነበሩትን የድሮ ሙዚቃ ቪድዮዎች ባየሁ ቁጥር አንድ ነገር ይገርመኛል ! ዘፋኞች በጣም የተጋነነ የእጅ እና የፊት እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፤ ለምሳሌ ፀሀየ ዮሀንስ ከነዋይ ደበበ ጋር አንዲት ማይክ ተካፍሎ በሚዘፍንበት ቪድዮ ውስጥ፤
“ ባቄላ ምርቱ እንጂ አያምርም ክምሩ
ተጫወች ልጫወት ምንድነው ማፈሩ “
ሲል በእጆቹ እንቅስቃሴ የባቄላ ክምርን ለተመልካቹ ለማሳየት መከራውን ያያል ! ይሄ ለምን አስፈለገ ልትል ትችላለህ! በዛን ዘመን የነበረው ትቪ ድምፁ ጥራት አልነበረውም ፤ ጠረጴዛ ላይ ተጎልቶ ደቅ ደቅ ደቅ ሲል መስታውት የተገጠመለት ጄኔተር ይመስላል ! እና ዘፋኞች ዘፈናቸውን በምልክት ቋንቋ እንዲያጅቡ ይገደዱ ነበር!

(የሰርፀ ፍሬ ስባሃትን አስተያየት አይቼ እቀጥላለሁ)

3 Comments

  • ሰለሞን መኮንን commented on August 16, 2020 Reply

    1ኛ

  • Hassen Muhe commented on March 8, 2021 Reply

    ይመችህ

  • Anonymous commented on June 4, 2021 Reply

    ጎሽ…
    ጥሩ ብለሀል የጤናውንስ ብትል
    “ማጣት እንደ ኩፍኝ ይጋባል ወይ
    እኔስ ግራ ገባኝ አወይ አወይ”
    አሸናፊ ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *