(ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ)
ላሎ ወደ መርሀባ ተጠጋና ምንጣፉ ላይ በጀርባዋ አንጋለላት። ከዚያ በእግሮቿ ማሃል በርከክ አለና ቁልቁል ተመለከታት። ፊቷ በላብ ተጠምቋል!! ትንፋሿ ቁርጥ ቁርጥ ይላል። እግሯን ብድግ አድርጎ ወደ ደረቱ ሳበው።
አንባቢ ሆይ! የወሲብ ታሪክ የምተርክልህ መስሎህ እግርህን በእግርህ ላይ ጭነህ በጉያህ ላይ የሚርመሰመሰውን ስሜት ለመጨቆን እየታገልህ ከሆነ ተሸውደሃል። 😉
ላሎ ረከቦት ጎዳና በሚገኘው “ቸኮልየት ሆቴል ” ውስጥ የጂምናስቲክ አስልጣኝ ሲሆን መርሃባ ከሰልጣኞች(ጅምጃሚዎች) አንዷ ናት።
ከላይ ያቀረብኩት ከስልጠናው የተቀነጨበ ትይንት ነው።
“ከማህፀን ሀኪምነት ቀጥሎ ወደ ሴቶች ገላ ባቋራጭ የሚያስጠጋ ሙያ ቢኖር የጂም አስልጣኝነት ነው”ይላል ምኡዝ።
እውነቱን ሳይሆን አይቀርም። የመርሃባን እግር ለመንካት ስንቱ በሩቅ ጎመዠ?! ስንቱ ሳይተኛ ቃዠ! ላሎ ግን ይሄው ሙያውን ተገን አድርጎ እንደ እዝን ቤት ንፍሮ ይዘግነዋል።
ላሎ ጠይም ከመሆኑ በቀር ሚካየል አንጀሎ የቀረፀውን የዳዊት ምስል ይመስላል። ጠይም ዘለግ ያለ ቢሆንም ጎራዴ አይታጠቅም። ደረቱ ጃንሜዳ ነው። ሆዱ እንደሸንኮራ አጥቅ አለው። ላሎ ለጥሬ ስጋ ያለው ፍቅር ከጠቅላይ ምኒስትሩ ይበልጣል። “ክትፎ ሲበላ በንጀራ ወይም በቆጮ ሳይሆን በስስ ጥሬ ስጋ እየጠቀለለ ነው “ይሉታል ምግበ- አበሮቹ።
መርሃባን ሳይወዳት አልቀረም። እኔና ሌሎች ጅምጃሚዎች አጠገቧ ከቆምን ዓይኑ ደም ይለብሳል።
መርሃባ ለጂም ከተመደበው ጊዜ ግማሹን የምታጠፋው መስታውት ፊት ቆማ በራሷ በመመሰጥ ነው። እንዲያውም አንዳንዴ ሳስበው ወደ ጂም የምትመጣው መስታወት እንደልብ ስለምታገኝ ይመስለኛል። ትንሽ ዱብ ዱብ ትልና እጆቿን ወገቧ ላይ አስቀምጣ የቁም መስታውቱ ፊት ግትር ትላለች። ለነገሩ እሷ መስታውት ያላየች ማን ይይ? እኛ እንኳ ይሄን ባጃጅ ፊት ተሸልመን : ይሄን የማር አቆማዳ የመሰለ ቀፈት ተሸክመን መስታውት ላይ እንጣዳለን።
” እኒህን በመሰሉ እግሮች ጨክነሽ ትሮጭባቸዋለሽ?” አልኳት አንድ ቀን ከምትሮጥበት ማሽን ስር ቆሜ።
ገልመጥ አረገችኝና ወደ ሩጫዋ ተመለሰች። ወድያው ግን የማጣርያ አስተያየት አየችኝና:-
“አንተ (ስሜን ጠርታ) አይደለህም እንዴ?”
“ነኝ”
መሮጫ ማሺኑን አረጋጋችውና ፊቷና አንገቷን በፎጣ አበሰች።
ለረጅም ጊዜ የምንተዋወቅ ያክል ስለኑሮና ስለመፃፍ አወጋን።
ደና አውርተን አውርተን ልናሳርግ ስንል እንዲህ አለች:-
“ይገርምሀል! አንድ ቆንጆ ድርሰት ካነበብሁ ብዙ ነገር አስባለሁ!..አንዳንዴ ደራሲው አልጋ ላይ እንዴት ይሆን ብየ እስከማሰብ እሄዳለሁ”
የተልባ ማሻው ሚካየል ያለህ! እንዲህ አይነት ልብና ጉያ የሚያግል ጨዋታ ከሰማሁ ስንት ዘመን አለፈኝ!! ልመልስላት ስሰናዳ ላሎ ተንደርድሮ መጣና ክንዴን ይዞ እየጎተተ ወሰደኝ ። ከዝያ ካዳራሹ ጥግ ላይ መቶ ኪሎ ብረት ቀንበር አሸክሞኝ ” ይሄንን ለሃያ ደቂቃ ስራ “ብሎኝ ወደ እሷ ተመለሰ።
ከቀንበሩ የሚያስጥለኝ ሰው ባይኔ ስፈልግ: በስተግራ ዴኔል የመሮጫው ማሽን ላይ የህልም ሩጫ ሲሮጥ አየሁት።
የሴራሊዮን ሰው መሆኑን ነግሮኛል: : እንደ ዶቅማ ፍሬ ደማቅ ጥቁር ነው። ለሀያ አመታት ያክል ምግቡን በባቄላ በሩዝ በፍራፍሬና ቅጠላቅጠል ብቻ ወስኖ ይኖራል ። ሳይፎርሽ በየቀኑ ጂም ይሰራል። ከራሰ በራነት የተረፈችውን ፀጉሩን ይላጫል። እናም ትኩስ መላጣውን ከነባር መላጣው ጋር በመቀላቀል ጎረምሳ መስሎ ለመታየት ይጣጣራል። ነጭ ጢሙን በላጨው ቁጥር ቶሎ ስለሚያቆጠቁጥ : ፊቱ የተጠረገ የድንጋይ ወፍጮ ይመስላል። የሚሮጠው ከርጅና ለማምለጥ ነው። ከርጅና ለማምለጥ የሚደረግ ሩጫ ልክ እንደማሽን ላይ ሩጫ ነው። ትፈጥናለህ። ላብህን ትዘራለህ። ግን ካለህበት ቦታ ፈቀቅ አትልም።
ዴኔየል ሁሌም ከድሜው በላይ ወጣት መሆኑን የሚያረጋግጥለት ሰው ይፈልጋል።
“አምሳ ስምንት አመቴ ነው። ብዙ ሰዎች ግን ያምሳ ስምንት ዓመት ሰው አትመስልም ይሉኛል” አለኝ አንድ ቀን ከጂም በሗላ ጎንለጎን ቁጭ ብለን እንፋሎት ስንጠመቅ።
“እውነታቸውን ነው” አልሁት።
ፊቱ በደስታ ወገግ አለ።
“የስንት አመት ሰው እመስላለሁ?”
” የስድሳ ስምንት”
በጣም ተናደደ።
ጥግ ላይ ወይዝሮ ሮዝ ገመድ ሲዘልሉ ይታየኛል። እንደ ድልህ ሙክክ ብሎ የቀላና ምቾት የጠገበ ፊት አላቸው። በኮረዳነታቸው ዘመን ሞዴል የነበሩ ሲሆን በ”ዘሚት ቅባት “ጠርሙስ ላይ ምስላቸው ይወጣ ነበር። እዚህ ላይ: የኮሎኔል አልፋ ሚስት መሆናቸውን መጠቆም ያለብኝ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ: ኮሎኔል አልፋ ጥሮታ ሲወጡ ከደመወዛቸው ቆጥበው ባጠራቀሟት ሳንቲም ረከቦት ጎዳና ዳር ባለ አምስት ፎቅ ህንፃ ሰርተዋል።
እንደሚታወቀው የመጀመርያው የባቡር ፕሮጄክት ከሸገር ወደ ናይሮቢ ሊዘረጋ የታቀደ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያ ሲያልፍ የኮሎኔሉን ህንፃ እንደሚነካ ተረጋገጠ። ሸማቹ ፓርቲ ህንፃውን አፍርሶ ኮሌኔሉን ማስቀየም ስላልፈልገ ፕሮጄክቱ ተከልሶ ካዲሳባ ወደ ጅቡቲ እንዲሆን ተወሰነ።
ላሎ ወይዘሮ ሮዝን እንዴት አርጎ ጂም እንደሚያሰራቸው ይጨንቀዋል። ያንድ ኮሎኔል ሚስትን ክብር ሳይነካ ማዘዝ የሚቻለው እንዴት ነው?
አንድ ቀን ጎንለጎን ደርድሮን የደቦ ስፖርት ሲያሰራን እኔን ” አቦ እግርህን አምቧትር” ብሎ ጮኸብኝ። ከዝያ ወደ ወይዘሮ ሮዝ ዞር ብሎ በትህትና እንዲህ ሲል ሰማሁት።
“የኔ እመቤት እግሮችዎን በየአቅጣጫው እንዲያሰማሩልኝ እጠይቃለሁ”
One Comment
ማምቧተር። ወይ አለመርሳት።