ጓደኛየ ዘፈን መስራት ካቆመ አስር አመታት ያለፈው ድምጻዊ ነው። ዋና ስሙ ፋኑኤል ሲሆን ለደህንነቱ ሲባል ” ዘነመ” እያልሁ እጠራዋለሁ፤ ከቀናት ባንዱ ሰንበት “ወለላ “ ምግብ ቤት በረንዳ ተቀምጠን አስተናጋጅ እንጠብቃለን፤ አንዲት እንዲያው በደፈናው የአፈወርቅ ተክሌን ስእል የመሰለች ሴት ከፊታችን ብቅ አለች።
“አድናቂ ነኝ”
“በጣም አመሰግናለሁ” አልኩ፤
“ፈርምልኝ”
“ምን ላይ ልፈርም?’
አንባቢያን ሆይ ! ባታምኑኝም ከመናዘዝ ወደ ሁዋላ አልልም፤ እየተሽኮረመመች “ጡቴ ላይ“ አለችኝ። እኔም ከኢትዮጵያ ባህል ጋር ላለመጋጨት፤ ከጡቷ ጋራ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ላለመቆራረጥ ፤ የጡት ማስያዣዋ ላይ ፈረምኩ።
“የት ነው እምትኖሪው?”
“ ሪችመንድ ነኝ! ከሁለት ሳምንት በሁዋላ አገር ቤት እሄዳለሁ”
“እቃ ይዘሽልኝ ትሄጃለሽ?”
‘ ኖ ፕሮብሌም! ይሄ ላንተ የማደረገው ትንሹ ነገር ነው “
“ለኔስ?” አለ ዘነመ፡:
‘ ቤቴ ራት እንድጋብዛችሁ ፍቀዱልኝ! ቆንጆ ጭቅና ጥብስ መስራት እችላለሁ”
“ደስ ይለናል” አለ ጓደኛየ ተሽቀዳድሞ፤
ትንሽ ቆይቶ “መጣሁ!“ አለና ሹልክ ብሎ ወጣ፤
“አግብቷል?” ስትል ጠየቀችኝ፤
“አራት ጊዜ አግብቶ ፈቷል ”
“አንተም ፈት እንደሆንህ ሰምቻለሁ፤”
“ ልክ ነሽ! ስራ ፈት ነኝ”
“ ሸበላ ነገር ነው”
“ ጠባዩስ ብትይ ! ዘንዶ ያለምዳል”
ወደ ፊልም ቢቀየር ሁለት ሲዝን የሚወጣው ወሬ ስናወራ ከቆየን በሁዋላ ፤
“ እኔ እምልህ እስቲ ስለ እቃው ንገረኝ” አለችኝ።
“ ጎን ለጎን ሆነን ስንሸና እንዳየሁት ከሆነ አስተማማኝ እቃ ነው ያለው “ አልኳት።
“ እኔ እንኳ የጠየኩህ አገር ቤት ትወስጅልኛለሽ ስላልከኝ እቃ ነበር ! ብቻ መረጃ አይናቅም”
ከማፈሬ የተነሳ የምመልሰው ቸግሮኝ ሳልጎመጉም ጓደኛየ ሁለት ኪሎ ስጋ እና አንድ ወይን ፤ ይዞ ተመለሰ;
እሳት ጎርሳ ፤ ጭስ ተፍታ ወቀሰችው፤
“አፒታይት እና ስጋ ከኛ ነው፤ ካንቺ ሙያ ብቻ ነው እሚጠበቅብሽ ” ብሎ አለዘባት ።
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ወደ ቤትዋ መንዳት ጀምራለች፡: እኔና ዘነመ በርሱ መኪና ተከተልናት ” ሸበላ ” ነው ያለቺውን ስነግረው “ ባትለኝም፤ ልጂቱ እንደተዝለፈለፈችልኝ ገና ከመጀመርያም አውቄዋለሁ፤ ቤት ስንደርስ እንደፈረደብህ የሆነ ምክንያት ፈልገህ ዞር ትላላህ” አለኝ።
“የት ነው ዞር የምለው ?” አልሁ ያለ የሌለ በሽቄ።
“ወይ ሞቴል ትይዛለህ ! ካልሆነ የፈረንጅ ደጀሰላም ፈልገህ ትተኛለህ ”
ሁለት ሰአት ያክል ነድተናል። የምትኖርበት ኮንደሚኒየም በር ላይ ስንደርስ መጥርያውን ተጫነቸው፤ በሩ ሲከፈት አንድ የጠወለገ ራስታ ሰውየ ከውስጥ ብቅ አለ። ከወገቡ በላይ የተራቆተው ሰውነቱ በንቅሳት ተዥጎርጉሮ የጥምቀት ሽመል ይመስላል፤ ሰላምታ እንኳ ሳይመጸውተን ስጋውንና ወይኑን ተቀብሎን ወደ ውስጥ ገባ፤ ተከትለነው ስንዘልቅ የጫማ፤ የሀሺሽ እና የድህነት ጠረን ተቀበለን።
ሰጋውን ከምኔው ጠብሶ አደረሰው?! አበላሉን ስመለከት፤ ላለፉት ሶሰት ቀናት እህል እንዳልቀመሰ መገመት አላቃተኝም፤ እኛን እንደ እንግዳ ቀርቶ እንደ ፖስተኛ እንኳ አልቆጠረንም፤
ዘነመ ፤ጥግ ይዛ ወይናችንን እምትቀመቅመውን ጉደኛ እየተመለከተ “ ሸኚን” የሚል ምልክት አሳያት፤
ሶስታችን ድምጻችንን አጥፍተን አንድ አራት ደረጃ ወረድን፤
ከጠጉሬ እስከ ጥፍሬ የወጠረኝን ሳቄን ለመቆጣጠርና የወዳጄን ፊት ላለማየት መታገል ጀመርኩ፤
ብዙ አልራቅንም፤ ዘነመ ርምጃውን ገታ አድርጎ ፤ ለመላው የህንጻው ነዋሪ በሚሰማ ድምጽ
“እናትሽ ትረዳና ባል እንዳለሽ ለምን አልነገርሽኝም?” ብሎ ጮኸባት!
ልጂቱ፤ዘና ፤ ረጋ ብላ የመለሰችውን ልጻፈውና ታሪክ ይፍረደው፤
“አገሩ super busy ስለሚያደረግ ብዙ ነገር ትዘነጋለህ! ባል እንዳለኝ ራሱ ትዝ ያለኝ አሁን ነው”