አዲሳባ እየሰፋች ነው፤ ከጥቂት አመታት በሁዋላ“ በአዲስአበባ አስተዳደር በአንኮበር ክፍለከተማ ነዋሪ ሆኑት አቶ በእውቀቱ“ የሚል ነገር መስማታችን አይቀርም፥ አያት ወደ እሚባለው ሰፈር ብቅ ካሉ የፈረስ ጋሪ፥ ባጃጅ እና ዘመናዊ መኪና ትከሻ ለትከሻ እየተጋፉ ሲያልፉ ያያሉ፥ ባንድ ከተማ ውስጥ ሶስት ክፍለዘመኖች፥ ጎንለጎን ይራመዳሉ።
ሀብታሞች በሀብት ከላይ ሀብት ጭነዋል ፥ድሆች የባሰ ድሀ ሆነዋል፥ የዛሬ ሶስት አመት ያንድ ሆቴል ባለቤት የነበረው ሰውየ ዛሬ ሶስት ቅርንጫፎች ከፍቷል! የዛሬ ሶስት አመት መጽሀፍ እሚያዞረው ልጅ ዛሬም መጽሀፍ አዟሪ ነው።
ከትናንት ወድያ። በከተማው ዘናጭ ከተባሉት ሬስቶራንቶች አንዱ ጎራ አልሁ፥ አዲስ ዩኒፎርም የተሰፋለት ዘበኛ፥ ከሸራ ጫማየ እስከ ጋሜየ ድረስ ገምግሞኝ ሲያበቃ፥
“ወዴት ነው?” አለኝ፥
“ወደ ምሳ“
ዘቡሌው ያለምንም እፍረት እንዲህ ሲል ጠየቀኝ፥
“መኪናህስ?”
“ትናንት ከዱባይ ተጭኗል፥አየሩ ጥሩ ከሆነ ነገ ጅቡቲ ይደርሳል”
ገባሁ፤
ምግብ ቤቱ ጠረጴዛ ላይ እንደ ሪፖርተር ጋዜጣ ዳጎስ ያለ ገጽ ያለ ሜኒው ተከምሯል፥ ይህንን ሲገልጥ ማን ይውላል?
“አስተናጋጅ”
“አቤት”
“ግማሽ ሽሮ ግማሽ ቲማቲም፥ ከስንግ ቃርያ ጋር፥ ስንት ሺ ብር ነው?”
በማግስቱ ፥ ካስፓልት ዳር ያለች፥ በቆርቆሮ የተከበበች መናኛ ምግብ ቤት ሄድኩ፥ ድንች ጥብስ በሚጥሚጣ ተበላ! የጀበና ቡናም ደርሶናል፥ ጥቂት ሰዎች በሰማያዊ ፕላስቲክ በርጩማ ላይ ተደርድረዋል፤ ካጠገቤ የተቀመጠ ሰውየ በወሬ ጠመደኝ። ንግግሩ ሳይሆን በካቲካላ የተመረዘ ትንፋሹ እጄን ባፌ አስጫነኝ!
“ስራህ ምንድነው?” አለኝ፥
“ጸሀፊ ነኝ”
“የመዝገብ ቤት ነው?”
ገላመጥሁት፥
“ስንት ልጆች አሉህ” ሲል ቀጠለ፥
“አልወለድሁም”
“ያልወለድክበት ምክንያት ምንድነው?”
“ከግብረስጋ ታቅቤ ስለምኖር ነው”
“ቡና ጠጣ”
“አሁን ጠጣሁ”
ግዴለህም ጠጣ”
“አልጠጣም”
“የይርጋ ጨፌ ቡና ነው”
“ለምን የይርጋ ዱባለ አይሆንም፥ አልጠጣም ካልሁ አልጠጣም”
በምልልሳችን መካከል ተንቃሳቃሽ ነጋዴዎች ጣልቃ ገቡ፥
-ነጭ ሽንኩርት! ነጭ ሽነኩርት!
-ሸንኮራ ያሰፈልጋል ፍሬንድ?
ጭራሽ የሆነ ሰውየማ ደርዘን ከዘራ ይዞ ቀረበኝ፥
“በዚህ ዘመን ከዘራ ገዝቼ ምን አደርገዋለሁ ዠለስ! ጨዋታው በስናይፐርና በዲሽቃ ነው“ አልኩት፥
“እንድትፋለምበት ሳይሆን እንድትመረኮዝበት ብየ ነው፤“ ሲለኝ፥
ስለ ኢኮኖሚ ግሽበት ማሰብ አቁሜ ስለ እድሜየ ግሽበት ማሰብ ጀመርኩኝ።