ራይድ ለመዲናይቱ አሪፍ ጸጋ ነው፤ ለብዙ ሰው ስራ ፈጥሮ የብዙ መንገደኞችን ኑሮ አቅልሏል። ራይድ የሚሰሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደኔ የክፍለሀገር ልጆች መሆናቸውን መርሳት አይገባም። ባለፈው አንዱ ባለ ቢትስ መጣልኝ፥ ጢንጥየ መኪና ናት፤ አራት ጎማ ያላት የዲዮጋን ቀፎ በላት፤ አሁን በመንሽ እግሩ ያዲሳባን አቧራ ሲቀዝፍ የሚውል እንደ እኔ ያለ ዘመን አይሽሬ እግረኛ ሰው መኪና ላይ ሙድ መያዝ ነበረበት? ሰው ምን ይለኛል አይባልም? ሆ!”
“ጋቢና ትገባለህ ወይስ ከሁዋላ ?” ሲል አማረጠኝ፥
የመኪናይቱን በር እንደ መርቲ ጣሳ ክዳን ከፍቼ፤ እንደ ሰርከስ ባለሙያ ተጣጥፌ ከሁዋላ ገባሁ፥ እንደ እውነቱ ከሆኑ የመኪናይቱ መላ አካልለሁለት የተከፈለ ጋቢና ቢባል ያስኬዳል፤ መኪናዋ ከመጥበቧ የተነሳ ከሾፌሩ ጋራ አንድ ቀበቶ ለሁለት አስረን መሄድ ጀመርን።
“የት ነው መዳረሻህ?”
“ቀበና ፥ሳንፎርድ”
“የት ጋ ነው እሱ ደሞ?”
“እኔም እንግዳ ነኝ፤ ባካባቢው ህብረተሰብ ርብርብ ልናገኘው እንችላለን”
ሼፌሩ በሰፈር መሀል እየነዳ የሆነ ቅያስ ላይ ሲደርስ አንድ ሸማግሌ አስቆመና አድራሻ ጠየቃቸው፥
“በዚህ ቀጥ ብልህ ሂድና ወደ ግራ ስትዞር ያፈንጉስ ነሲቡን ድልድይ ትሻገራለህ” ብለው ጀመሩ፤
“አሀ” አለ ሹፌሩ፥
“ድልድይ ማለት፤ ከገደል ገደል የተዘረጋ ጥፍጥፍ ብረት፤ ጣውላ፥ አለት፥ ወይም ግንድ ሊሆን ይችላል”
“ገባኝ”
“አፈንጉስ ነሲቡ ማለት ደግሞ ባጤ ምኒልክ ዘመን የታፈሩና የተከበሩ ዳኛ ናቸው“ ቀጠሉ፤ አረጋዊው፤
“ሰውየው በሙስናም የታወቁ ነበሩ” የሚል ጨመርሁ፤
(በታሪክ ዙርያ የመከራከር ስር የሰደደ ሱስ አለብኝ)
“የተጨበጠ ማስረጃ አለህ ወይስ ከኪስህ እያወጣህ ነው እምትናገረው” አሉኝ ሰውየው ደማቸው ፈልቶ፤
እኔና ጠቁዋሚው ሰውየ በታሪክ ዙርያ ስንጨቃጨቅ ሾፌሩ ትግስቱ አልቆበት ከጎረቤት ሹፌር ተበደረ፤
“ያፈንጉስ ነሲቡን ድልድይ ካለፍን በሀዋላስ?” አለ፥ ሹፌሩ በመጨረሻ፥
፡ ያፈንጉ ነሲቡን ድልድይ ካለፋችሁ በሁዋላ ያፈንጉስ ነሲቡን አደባባይ ትዞሩታላችሁ”
“ከዞርን በሁዋላስ?”
“ደርቡት!”
በመጨረሻ፥ ሳንፎርድ አካባቢ ደረስኩ፤ ትንሽ ተራምጄ አንዱን ሎተሪ አዟሪ አስቁሜ
“ዠለስ እዚህ አካባቢ፤ ንግድ ባንክ አለ?”
“ልታስገባ ነው ልታስወጣ?”